የADRA ኢትዮጵያ እና የኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ የአረንጓዴ ኢነርጂ ፕሮጀክት በስኬት ተጠናቀቀ::

  • June 5, 2026
  • Comment 0

ADRA Ethiopia  ከኢትዮ-ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ላለፉት 3 አመታት ሲተገብር የቆየውን የVQEP/Green Energy TVET Project Phase II ፕሮጀክት አጠናቆ የማጠቃለያ መድረክ አካሄደ::

ፕሮጀክቱ ባለፉት አመታት በአስተዳደራችን ለመጀመርያ ጊዜ ከ130 በላይ ወጣቶችን አዲስና ተፈላጊ በሆነ የሙያ ዘርፍ(Solar PV Installation & Maintenance) ላይ አሰልጥኖ ወደ ስራ እንዲገቡ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ያስታወሱት የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ሲሆኑ ፕሮጀክቱ በስልጠናው ዘርፍ ለፈጠረው አቅም ፣በከተማና በገጠር ላከናወነው የስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም የSolar ኢነርጂን ተደራሽ በማድረግ የGreen TVTን በተግባር እንድናሳይ ላከናወናቸው ተግባራት በቢሮውና በአስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል::

ADRA Ethiopia በሀገሪቱ ብዙ ቦታዎች ላይ ይንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም ድሬዳዋን ተደራሽ ያደረገው በዚህ ፕሮጀክት መሆኑን ያስታወሱት የኮሌጁ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ ሲሆኑ ከዚህ በፊት ያልነበሩ እንቅስቃሴዎችና ብዙ በረከቶችንም ወደ ተቋማችን ይዞ የመጣ ፕሮጀክት ነው ያሉ ሲሆን በGreen Energy ላይ ግንባር ቀደም ሆነን እንድንሰራ ፈር የቀደደልን ልዩ ፕሮጀክት ነውም ብለዋል::

የኮሌጁ ዲን አክለውም ፕሮጀክቱ ያስቀመጠውን ግብ በመምታት ረገድ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም እንደነበረው አስታውሰው ፕሮጀክት የራሱ የጊዜ ገደብ ያለው በመሆኑ ዛሬ ማጠቃለያ ብናደርግም በቀጣይ በጋራ የምንሰራቸው በርካታ ስራዎች በመኖራቸው እንደ ተቋም ደስተኞች ነንም ብለዋል::

ADRA በ120 ሀገሮች ውስጥ የሚቀሳቀስ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንደሆነ ያስታወሱት ADRA Ethiopia የProgram Director ዶ/ር ዘሪሁን አዋኖ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ላለፉት 3 አመታት ምበተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ ሰው ተኮር ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ገልፀው በውቢቷ ድሬዳዋ በነበረው የፕሮጀክቱ ሂደትና የተመዘገበው ውጤት እጅግ የሚያኮራና የአስተዳደሩንም ሆነ የኮሌጁን አመራሮች ቁርጠኝነት የተመለከቱበት እንደነበርም ገልፀዋል::

በማጠቃለያ መድረክ ላይ የADRA Ethiopia ፕሮጀክት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያከናወናቸውን ቁልፍ ተግባራትና ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች በፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ በየነ አማካኝነት ለባለድርሻ አካላት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም በፕሮጀክቱ ሂደት ላይ በኮሌጁ ጥናት በማድረግ የመጣውን ለውጥ የሚገመግም ሰነድም በመድረኩ ቀርቦ ገለፃ ተደርጎበታል::

በመጨረሻም የፕሮጀክቱ አመራሮች ከስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው እና ከኮሌጁ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ እጅ ላበረከቱት አስተዋፅኦ የእውቅና ሰርተፊኬትና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል::

የADRA ኢትዮጵያ ካንቲር ዳይሬክተር (ADRA Ethiopia Country Director) አቶ ዲማ ሳባ እንደገለፁት
ከጀርመን የልማት ትብብር ተቋም(BMZ) እና በADRA Germany በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር ከኢትዮ-ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ እና ከሌሎች ቁልፍ ባለ ድርሻ አካላት በመተባበር ሲተገበር የነበረው የVQEP/Green Energy TVET Project Phase II ፕሮጀክት በርካታ ስኬቶችን በማስመዝገብ በዛሬ እለት ፍፃሜውን አድርጏል::

የኢትዮ-ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
ግንቦት 20/2018 ዓ.ም
ድሬዳዋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *