
የኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከአድራ (ADRA) ኢትዮጵያ ጋር በመሆን በሶላር (በፀሐይ ሀይል )የሚሰሩ የተለያዩ የምርት ውጤቶችን የሚያስገኙ መሳሪያዎችን በመስራት በይፋ አስመርቆ ሥራ አስጀምሯል።
በወቅቱም ከጀርመን እና ከኢትዮጵያ አድራ የመጡ የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ፤ የኮሌጁ አመራሮች እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የመጡ ኃላፊዎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑት በማህበር የተደራጁ ሰራተኞችም ተገኝተዋል።
በምርቃት መርኃግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ አድራ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ወደ ኮሌጁ ከመጣ በኋላ መጀመሪያ ላይ በፀሐይ ኃይል ( በሶላር ) የሚሰራ ወፍጮ በመስራት ይፋ ማድረጉን አስታውሰው አሁን ደግሞ ለኮሌጁ እና ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚጠቅም በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓንፕ ፣ የዘይት መጭመቂያ መሳሪያ እና የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸው በማኅበር ተደራጅተው የሚጠቀሙበት የመኪና ማጠቢያ (ላቪያጆ ) በመስራት ርክክብ እንዳደረጉ ገለፀዋል።
ዲኑ አያይዘውም በተለይ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ በፀሐይ ኃይል የወጣው ውሃ ኮሌጁ የነበረበትን ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ችግር ቀርፏል ነው ያሉት። ውሃውም ከኮሌጁ አልፎ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብሎም በግቢው ውስጥ በመኪና አጠባ ሥራ ለተደራጁት ማኅበራት የስራ እድል መፍጠር የተቻለበት አቅም ፈጥሯልም ብለዋል።
ዲኑ አድራ ኢትዮጵያም ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የአድራ ኢትዮጵያ ዳሬክተር ዶ/ር ዘሪሁን አዋኖ በወቅቱ እንደገለፁት የድሬዳዋ ኢትዮ ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በፀሐይ ኃይል አጠቃቀም በኩል በገጠርም በኮሌጁም እየደረገ ያለው ስራ እጅግ በጣም የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የፀሐይ ኃይል ማመንጫውን በዘላቂነት ለመጠቀም ኮሌጁ በአጫጭር ስልጠና ያስተማራቸውን የሶላር ጥገናና ተከላ ባለሞያዎችንም በማፍራት በማህበር በማደራጀት ወደስራ ማስገባቱ የሚደነቅና ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ይህም በፀሐይ ሓይል የሚሰራ ስራ መቀጠል አለበት በማለት ጨምረው ገልፀዋል።
የጀርመኑ አድራ ዳሬክተር አቶ ዳዊት መሐሪ በድሬዳዋ ኢትዮጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ያየነው ተጨባጭ ተግባር ተደስተናል። በቀጣይም በሌላ ፕሮጀክት አብሮነታችን ይቀጥላል ብለ፥ ይህ ስራም ኮሌጁ ከራሱ አልፎ አሁንም ለሌሎች መትረፍ አለበት በማለት አሳስበዋል።
በመርኃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩት መሳሪዎች ርክክብና ስራ ማስጀመሪያ ፊርማ የተከናወነ ሲሆን እንዲሁም በመኪና አጠባ ለተደራጁት አካል ጉዳተኞች የስራ ማስጀመሪያ የሚሆን አጫጭር ስልጠና ስልጥነው ያጠናቀቁበት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
የኢትዮ-ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ
መጋቢት 25/2018 ዓ.ም
Telegram https://t.me/EIPC2001
Facebook https://www.facebook.com/share/19wDiZAD7x/?mibextid=wwXIfr
































